የልጆች ጥበቃ ቃል ኪዳን መግቢያ ሰነድ


አድማስ

የልጆች ጥበቃ ሰነድና የቃል ኪዳን መግቢያ ፅሑፍ ሁሉንም ከኮምፓሽን ኢንተርናሽናል ጋር ግንኙነት ያላቸው፣ የኮምፓሽን ኢንተርናሽናል አጋሮች፣ ተወካዮች ማለትም የቦርድ አባላትና ሰራተኞች፣ በጎ ፈቃደኞች፣ ኮንትራት ሰራተኞች፣ አለም አቀፍ ተባባሪዎችና አጋር አብያተ ክርስቲያናት እንዲሁም ጎብኚዎች ከተጠቃሚዎች ጋር በሚኖራቸው ቀጥተኛ ግንኙነት ወቅት ሊያሳዩት የሚገባውን  የሥነ ምግባር መመሪያ የያዘ ነው። ይህ መረጃ በኮምፓሽን ኢንተርናሽናል የጸደቀውን የልጆች ጥበቃ ሰነድ አስመልክቶ በአለምአቀፍ ደረጃ ሊኖር የሚገባውን አስፈላጊ የሥነ ምግባር ደንብ ያትታል። የሥነ ምግባር ደንቡ ከተጠቃሚዎች ጋር በሚኖር ግንኙነት ሁሉ መታየት ያለበትን አግባብነት ያለው ባህርይ በዝርዝር ያቀርባል።


ሀገር አቀፍ ቢሮዎችና አለም አቀፍ አጋሮች በራሳቸው አውድ  ሊተረጉሙት፣ አባባሉን ሊያብራሩት፣ አውደገብ ሊያደርጉት ወይም በዚህ ጽሑፍ ውስጥ ያሉ የግድ አስፈላጊ የሆኑ ሀሳቦች ሳይጓደሉ ተጨማሪ ሀሳብ ሊያካትቱ ይችላሉ። የቃል ኪዳን ሰነዱና ቃል መግቢያ ጽሑፉ በማንኛውም ሁኔታ ውስጥ ራሳቸውን ችለው ሊቀርቡ እንጂ  ከሌሎች የሚወጡ ደንቦች ወይም መመሪያዎች ጋር ተዳብለው መውጣት የለባቸውም። 


ሥልጣን

የልጆች ጥበቃ ሰነድና ቃል ኪዳን መግቢያ ጽሑፍ ሥልጣን በቦርድ መመሪያው 5.2.1 እና በአስተዳደር መመሪያው 102 ‘ዓለም አቀፍ የልጆች ጥበቃ’ ውስጥ ሊገኝ ይችላል።  እነዚህ ፖሊሲዎች የልጆች ጥበቃን አስመልክቶ ከልጆች ጋር ቅርርብ ለሚፈጥር ሰው ሊዘጋጅና ሊተገበር ያለበትን አስፈላጊ የሥነ ምግባር መመሪያ  ያሰቀምጣሉ። የልጆች ጥበቃ ቃል ኪዳን ሰነድ የሚፈርም ሰው ሁሉ በቃል ኪዳን ሰነዱና በሥነ ምግባር መመሪያው ላይ ጥልቅ እውቀት ሊኖረው ያስፈልጋል። የአስተዳደር መመሪያው ደግሞ ይህንን ቃል ኪዳን መጣስ የሚያስከትለውን ቅጣትና ሌሎች ከልጆች ጥበቃ ጋር ተያይዞ  ‘ለሚወሰድ የዲሲፕሊን እርምጃ ወይም የሥራ ውል ወይም ግንኙነት መቋረጥ መሰረት የሚሆኑ እርምጃዎችን ’ ያትታል። 


የሥነ ምግባር ደንብ

ተቀባይነት ያላቸው ሥነ-ምግባራት

  • የፆታ፣ የእድሜ፣ የዘር፣ የእምነት፣ የባህል፣ ልዩ ፍላጎት (አካል ጉዳትን)ና ማህበራዊ ሁኔታዎችን መሰረት የሚያደርግ ልዩነት ሳላደርግ ለሁሉም ልጆች አግባብነት ያለው ክብርና አክብሮትን አሳያለሁ፤ የኢየሱስንም ፍቅር እገልጥላቸዋለሁ።።
  • ልጆች እንዲተገብሩ የምጠብቀው ነገር እድሜያቸውንና ችሎታቸውን ያገናዘበ መሆኑን አረጋግጣለሁ። (ለምሳሌ የ3 ዓመት ልጅ ሲደክመው መሰላቸትን ቢያሳይ ጤናማ መሆኑን ሆኖም፣ ታዳጊ ልጆች ቢደክማቸው እንኳን ስሜታቸውን በአግባቡ መያዝ እንዳለባቸው መጠበቅ እንደሚገባ)።
  • ከፕሮጄክት ተጠቃሚዎች ጋር የማደርገው ተግባቦት ደረጃ ሁሉ የልጆችን እድሜ መሰረት ያደረገ መሆኑን አረጋግጣለሁ።
  • በሕግ የሚፈቀደውን የሥነ ምግባር ደንብ መሰረት ያደረገ ሆኖ፣ የፕሮጄክት ተጠቃሚ ልጆችን በአካል ከማግኘቴ በፊት ከወንጀል ነፃ መሆኔን የሚያረጋግጥ ወረቀት ከፖሊስ አቀርባለሁ። (ቢያንስ አንድ ሰራተኛ የቅጥር ውል ሲፈፅም ይህንን እንዲያቀርብ መጠየቅ አለበት)
  • ከፕሮጄክት ተጠቃሚዎች ጋር የማከናውነውን ልዩ ልዩ ተግባራት ሁሉ በግልፅ በሚታይ ቦታ የማደርግ ሲሆን፣ ተግባራቱን ከእይታ በተሰወሩ ቦታዎች በማከናውንበት ጊዜ ቢያንስ  እውቅና የተሰጠው  አንድ አዋቂ  በቦታው መኖሩን አረጋግጣለሁ።
  • በልጅ ላይ ጥቃት ተፈፅሞ ካየሁ/አንድ ልጅ አደገኛ ሁኔታ ውስጥ መሆኑን አብሮኝ ከሚሰራ ፣ አጋሮች ወይም ሌሎች ተወካዮች ከሰማሁ እንዲሁም ልጅ ራሱ ከነገረኝ ጉዳዩን ቸል ሳልል ወዲያው ለሚመለከተው ሰራተኛ ወይም ለሚመለከተው የመንግሥት አካል አሳውቃለሁ። ይህ ልጅ ካለበት አስቸጋሪ ሁኔታ እንዲወጣ በእኔ አቅም የሚቻለውን ሁሉ አደርጋለሁ። 
  • በምርመራው ውስጥ የተካተቱ አካላትን ምስጢርና ክብርን በማሰብ የልጆች ጥበቃ ምርመራዎች ጋር የተያያዙ መረጃዎችን በምስጢር እይዛለሁ።
  • አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ፣ ከልጆች ጥበቃ ጋር የተያያዘ ምርመራ እንዲደረግብኝ እስማማለሁ፣ ምርመራው እስኪጠናቀቅም ድረስ የሚያስፈልጉ መረጃዎችን አቀርባለሁ።
  • ልጆች የሚከበሩበትና መብቶቻቸውንና ሀሳባቸውን መናገር የሚችሉበትን ከባቢ በመፍጠር አስተዋፅዖ አደርጋለሁ።
  • ማህበራዊ መገናኛ ብዙሃንን ጨምሮ ከተጠቃሚዎች ጋር በሚደረግ የተግባቦት ሂደት ሁሉ የኮምፓሽን መመሪያን እከተላለሁ።
  • ልጆችን ፎቶ እና ቪድዮ በማንሳት ወቅት የሰው ክብር መመሪያን አከብራለሁ(ለምሳሌ አግባብነት ያለው አለባበስ የለበሱ ልጆችን ብቻ ማንሳት፣ ቪዲዮ እየተነሱ መሆናቸውን እንዲያውቁ ማድረግ ወዘተ)።
  • በአቀራረቤ፣ በንግግሬ፣ በድርጊቴ ለተጠቃሚዎች፣ ለቤተሰቦቻቸው፣ ለባህላቸውና ለመብታቸው በሚሰጠው መመሪያ መሰረት አክብሮትን የሚያሳይ ባህርይን እላበሳለሁ።

ተቀባይነት የሌላቸው ተግባራት

  • እድሜዋ የቱንም ያህል ቢሆን፣ከፕሮጀክት ተጠቃሚ  ልጅ ጋር የፍቅር ግንኙነት አልፈጥርም፣ ወሲብ ነክ ድርጊት አልፈጽምም፣እንዲሁም በጋብቻ አልጣመርም።
  • የሀገሪቱ ሕግ የሚፈቅድ ቢሆን እንኳን ወሲብ ነክ የሆኑ ድርጊቶችን ከ18 ዓመት በታች ከሆኑ ልጆች ጋር አላደርግም።
  • በማንኛውም አሳፋሪና ልጆችን በሚጎዳ ንግግር፣ ስሜታዊ ጥቃት በሚያደርስ  ወይም ልጆችን በማታለል ( ማማለል) ለወሲባዊ ማነሳሳት በፍጹም አልሳተፍም።
  • አግባብነት በሌለው ወይም በባህሉ ተቀባይነት በሌለው ሁኔታ ተጠቃሚ ልጆችን አልነካም (ለምሳሌ መሳም፣ማሻሸት፣ወደላይ ማንሳት መሸከም ወዘተ ሊጨምር ይችላል)።
  • ለመቅጣት በሚል ሰበብ ልጅን በበትር አልመታም (ይህም በአለንጋ መግረፍን፣ በዱላ መምታትን፣ በጥፊ መማታትን፣ ከባድ አካላዊ ቅጣቶችንና ሌሎች የድብደባ ቅጣቶችን ያጠቃልላል)።
  • ለሕይወት አስጊ ሆኖ ፈጣን ጉዞ በሚያስፈልግ አገዳጅ ሁኔታ ውስጥ  ካልሆነ በስተቀር እውቅና የተሰጠው ሌላ አዋቂ በሌለበት ከተጠቃሚ ልጅ ጋር ብቻዬን ጉዞ አላደርግም።
  • በማንኛውም ልጅ  ላይ ጥቃት በሚያደርስበት መልኩ የሥራ ቅጥር አልፈጽምም፣የልጆችን ቅጥር ሥራ በሚመለከትም የሀገሪቱን ሕግ አከብራለሁ።
  • አንድን ተጠቃሚ፣ አሳዳጊዎቻቸውን እንዲሁም ቤተ ክርስቲያንን ተቀባይነት ካለው መመሪያ ወይም ከጉብኝት  ደንብ አግባብ ውጭ አልጎበኝም።
  • ፈቃድ ቀድሜ ሳላገኝ፣ የኮምፓሽን ሰብዓዊ  ክብር መመሪያን በሚፃረር መልኩ ስለተጠቃሚ ልጅና ቤተሰብ የግል መረጃ ለምሳሌ እንደ አካላዊ፣ አዕምሯዊ ወይም ስሜታዊ፣ ገንዘብ ነክ፣ የጥቃትና ብዝበዛ  ታሪክ ጋር  የተየያዙ መረጃዎችን አልሰበስብም፣ የተጠቃሚውን ወይም የቤተሰቡን መኖሪያ አካባቢና መንደር በፎቶግራፍ ላይ የሚያመለክት ምስጢራዊ መረጃዎችንም አላወጣም። እንዲሁም እነዚህን የመሳሰሉትን ይዘቶች በሌሎች ለሕዝብ በሚታዩ የህትመትና ዲጂታል መረጃዎች ማውጣትንም የሚያካትት መሆኑን እገነዘባለሁ።
  • በማንኛውም ሕጋዊነት የሌላቸው የልጆችን ደህንነት በሚጎዱ ወይም በልጆች ላይ ጥቃት የሚያደርሱ ተግባራት ይህም የልጆች ብዝበዛ፣ የልጆች ዝውውር፣ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችና ለመናፍስት አምልኮ ሲባል በልጆች ላይ በሚደርስ የጥቃት ልምምዶች አልሳተፍም።

የቃል ኪዳን ሰነዱንና የሥነ ምግባር መመሪያውን መገንዘቤን እንደሚከተለው አረጋግጣለሁ

እኔ፣_______________________________________፣ ከዚህ በታች በተዘረዘሩት ሀሳቦች መስማማቴን አረጋግጣለሁ:- 

  • በኮምፓሽን የተዘጋጀ የልጆች ጥበቃ ቃል ኪዳን ሰነድ ኮፒ ተቀብያለሁ።
  • የቃል ኪዳን ሰነዱ ከኮምፓሽን ኢንተርናሽናል  ጋር ባለኝ አገልግሎት፣ ተሳትፎ እና ከኮምፓሽን ጋር ባለኝ የሥራ ግንኙነት ከኔ የሚጠበቀውን ሥነ ምግባር እንደሚገልጽ ተገንዝቤአለሁ።
  • የቃል ኪዳን ሰነዱን አንብቤ ይዘቱን ሙሉ በሙሉ ተረድቻለሁ።
  • የቃል ኪዳን ሰነዱን ትርጉምና አተገባበርን በሚመለከት ሥልጠና ተሰጥቶኛል። 
  • በዚህ ሰነድ ውስጥ ያልገባኝን ሀሳብ አስመልክቶ ጥያቄ የመጠየቅ እድል የተሰጠኝ መሆኑን አረጋግጣለሁ።
  • ይህንን የቃል ኪዳን መግቢያ ሰነድ ጥሼ ብገኝ የኮምፓሽን የቅጣት  እርምጃ ይኸውም  ከሥራ መባረርን ጨምሮ የአጋርነት መቋረጥ፣ የልጅ ረዳትነት መቋረጥ እንዲሁም ከኮምፓሽን ጋር የሚኖረኝ የትኛውም ዓይነት የሥራ ግንኙነት መቋረጥ እንደሚያስከትልብኝ መገንዘቤን አረጋግጣለሁ።
  • ምንም ዓይነት የዚህ ቃል ኪዳን ጥሰት  የፍትሀብሔር/ወንጀለኛ መቅጫ እርምጃ እንደሀገሪቱ ሕግና እንደኮምፓሽን  መመሪያ እንዲሁም (የውጭ ዜጋ ሲሆን፣ከሀገር ውጭ የሚጓዙ የአሜሪካ/የሌሎች አጋር ሀገራት ዜጎችን የሚመለከት) የቅጣት እርምጃ እንደሚያስወስድብኝ እገነዘባለሁ።

እኔ _______________________________________________ ከኮምፓሽን ሰራተኞች፣ ተጠቃሚዎችና ከኮምፓሽን ጋር የሥራ ግንኙነት ካላቸው ሌሎች ሰዎች ሁሉ ጋር በሚኖረኝ ግንኙነት በዚህ  የልጆች ጥበቃ የቃል ኪዳን መግቢያ ሰነድ ልመራ  ቃል እገባለሁ።